FREEDOM 4 ALL ETHIOPIANS

FREEDOM,DEMOCRACY.JUSTICE.AND UNITY FOR ALL ETHIOPIANS …by DANIEL TESFAYE

የደም አፍሳሾች ሸንጎና የህወሃት የዘር ፍጅት አዋጅ በወልቃይት ጠገዴ ላይ

በጎሹ ገብሩ፣ አባይ መንግስቱ፣ ገብሩ ማማይ፣ ቻላቸው አባይ፣ አበራ አታላይ፣ አብዩ በለው

“ወልቃይት የትግራይ ነው ! የአማራነት ጥያቄው በዚህ የማያቆምና ተጠናክሮ የሚቀጥል ከሆነ የማያዳግም እርምጃ እንወስዳለን…!”

አቶ አባይ ወልዱ

“የወልቃይት ጉዳይ ክልል አንድን እንጂ ማንንም አይመለከተውም፤ ውሳኔውም ሊሆን የሚችለው የክልል አንድ ብቻና ብቻ ነው፡፡”

ዶ/ር ደብረ ፂዮን ገ/ሚካኤል

“የወልቃይት አማራ መፍትሔ አፈላላጊ አካሉን በተደጋጋሚ አነጋግረናቸው በተፈቀደላቸው ህገመንግሥት ተጠቅመው መስራት ያልቻሉና ይልቁንም ከውጭ ካለው ፀረ ሰላም ኃይል ጋር በመሆን መንግሥትን በኃይል ለመናድ ከቆመ አካል ጋር እንደወገኑ፣ እኛንም የወያኔ ተላላኪዎች፤ ሆዳሞች፤ ቅጥረኞች እያሉ እየሰደቡን የሚገኙ ሲሆን፣ ከውጭ ያሉት ኃላፊዎቻቸውም በየሚዲያው እየቀረቡ የስድብ ናዳ ያወርዱብናል፤ በአውስትራልያና በአሜሪካ ትልልቅ ሰብሰባ እየጠሩ ሲያወግዙን እንደሚውሉ ደርሰንበታል፤ በተለይ አውስትራልያ ተጠርቶ በነበረው ሰብሰባ የኤርትራ ባለስልጣን በመጋበዝ ከኤርትራም በኩል እርዳት ሊደረግላቸው ቃል እንደተገባላቸው አረጋግጠናል። ድርጅታችን ህወሃትም ያማያዳግም ቅጣት ሊሰጣቸው ይገባል”

አቶ ፈረደ የሺወንድም

Gonder, Welkait Ethiopia Map

ይህ ሁሉ የሃሰት ውንጀላ፣ ገደብ የለሽ ዛቻና፣ ማስፈራሪያ የሚዥጎደጎደው ለባዕዳን ወራሪ ጦር እንዳይመስልዎ፤ ወይም ለፈረደባቸው የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አይደለም፤ ይልቁንም እኒህ ፍጹም ዘግናኝና ማባሪያ የሌላቸው የዘር ፍጅት አዋጆች የሚጎርፉትና የጦርነት ክተት ነጋሪት የሚጎሰመው በወልቃይት ጠገዴ ለመሸገ የISIS ወይም የአልሸባብ ክንፍ ላይም አይደለም። በሰላማዊና ንጹሃን ኢትዮጵያውያን ላይ! በጀግናውና በኩሩው የወልቃይት ጠገዴ ተወላጅ አማራዎች ላይ እንጂ!

በአለፉት ሁለት ሳምንታት የህወሃት የከፍተኛ ባለስልጣናትና ካድሬዎች ከፍተኛ ምስጢራዊ ስብሰባዎች በትግራይ፣ በወልቃይትና፣ በጎንደር በዝግ እያደረጉ እንደሚገኙ እንሰማለን። እነዚህ አስፈሪና አስጨናቂ የሚመስሉና ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግላቸው ስብሰባዎች የሚደረጉት ሃገርን ከውጭ ወራሪ ጠላት ለመከላከል ወይም ህዝብን ከአስከፊውና ከብልሹው የህወሃት መንግስት አሰራር ለማላቀቅ ሳይሆን የወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ ለአለፉት 25 ዓመታት በሃይልና በእብሪት የተጫነበትን ትግሪያዊነት ባለመቀበል የአማራ ማንነቱን ለማስከበርና ወደ ጎንደር/አማራ የአስተዳደር ክልል እንዲካለል በሰላማዊ መንገድ የሚያደረገውን ህዝባዊ  ጥያቄና ትግል በጦር ሃይልና በህወሃታዊ ግፍ ለመጨፍለቅ የሚደረግ የደም አፍሳሾች ሸንጎ ነው።

ይድረስ ለኢትዮጵያ ህዝብ !

የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ! ንጹሃንና ሰላማዊ ልጆችህን በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በኦጋዴንና፣ በጎንደር በአራቱም የሃገሪቱ አቅጣጫ በአምባገነኑ የትግራይ ነፃ አውጭ ቡድን የጥይት አረር በየመንደሩ መውደቀቻው ሳያባራ፤ እነሆ ይህ የኢትዮጵያውያንን ንጹህ ደም በከንቱ በማፍሰስና ሃገራችንን በማተራመስ የሚተጋው እኩይ ቡድን የወልቃይት ጠገዴ ተወላጅ አማራዎችን ንጹህ ደም ዛሬም እንደገና ለማፍሰስ የጦርነት ነጋሪት እያስጎሰመ ይገኛል።

አገር ወዳዱ ኢትዮጵያዊ ሆይ! እስከመቼ በገዳዮችህ ላይ ትታገሳለህ? እስከመቼስ የልጆችህ ንጹህ ደም በሃገራቸው ምድር እንደጎርፍ መፍሰስ አይገድህም? እስከመቼ ሃገርህ በጥቂት የዘረኞች ቡድን የዝርፊያና የመስፋፋት አባዜ ምክንያት ቤትህ ሲፈርስ ዝም ብለህ ታያለህ? እስከመቼስ ቀዬህ በወጣት ልጆችህ ስደት ሲፈታ እያየህ በዝምታ ስትቆዝም ትኖራለህ? ኃረ እስከመቼ ነው የወልቃይት ጠገዴ ወገኖችህ ሰቆቃ የማይገድህ? እስከመቼስ ነው ህወሃት በእኛ ላይ የሚያደርሰውን እልቂት “በቃ” የማትለው? ጆሮህንስ በጩኸታችን ላይ የምትዘጋው እስከመቼ ይሆን?

እነሆ አሁንም እኛ የወልቃይት ጠገዴ ተወላጆች ወደ አንተ ወደ ወገናችን እንጮኻለን! ዛሬ ህዝባችን ድጋፍህንና አጋርነትህን አጥብቆ ይሻል! የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ጠላት የሆነውን የትግራይ ነፃ አውጭ ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አምርረህ ትታገለው ዘንድ ታሪካዊ ጥሪ አቅርበንልሃል! ዛሬ ነገ ሳትል ለነፃነትህ ዘብ ቁም! ከኦሮሞ ወጣቶች ጎን በመቆም፣ ከጋምቤላ ግፉአን ጎን በመቆም፣ ከእኛ ጋር በመቆም ለጋራ ነፃነታችን እንታገል ዘንድ ሃገራዊ ጥሪ አቅርበንልሃል!

ይድረስ ለአማራ ህዝብ !

የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊንት ጠላቶች ተላላኪ የሆኑትና ኢትዮጵያን የማፈራረስና ህዝቦቿን የማተራመስ ተልዕኮ እያስፈፀሙ የሚገኙት  ህወሃትና አጋሮቹ በቅድሚያ ያነጣጠሩት ጌቶቻቸው አደራ በሰጧቸው በአንተ በ“አማራው” ላይ ነው። አንተ የባዕዳን ጭንቀት ነህና ለአለፉት 25 ዓመታት ከኤርትራ እስከ ሞያሌ፣ ከኢሊባቦር እስከ አፋር – ዙሪያ ገባውን በሃገር ላይ ትሳደድ ዘንድ ያለርህራሄ ተዘመተበህ። አንተን ለማሳደድ ሲባል ኢትዮጵያዊው ሁሉ ጎረቤቱን፣ አብሮ አደጉን፣ ትዳሩን፣ ይባስ ብሎ እራሱን ጭምር እንዲፈራ ተደረገ። ብሔረ-አማራ!

ለህወሃትና መሰሎቹ የዚህ አማራ የሚባል ምናባዊ ጠላት ባህሉም ሆነ ቋንቋው ወይም መኖሪያ ቦታው በውል አይታወቅም። ሲያሻቸው ከኤርትራ አልያም ጋምቤላ ውስጥ ይፈልጉታል፣ ወይም ከቤንሻጉል ያባርሩታል፣ አልያም ጉራፈርዳ ገደል ውስጥ ይጨምሩታል፣ ወይም በበደኖ እንደ በግ እያስጓጎሩ ያርዱታል፣ ከቤንች ማጂ በካሚዮንም እንደ ሸቀጥ እየጫኑ አንደ ምናምንቴ የትም ይደፉታል … ብቻ የትም ይፈለጋል፣ በተገኘበት ማንም ምንም ያደርግበታል።

ችግሩ ደግሞ አንተ እራስህን የምታውቀው በኢትዮጵያዊነትህ ዝቅ ሲል ደግሞ በጎንደሬ፣ በጎጃሜ፣ በወሎዬ፣ ወይም በሸዋነትህ በመሆኑ፤ትውልድህም፣ እድገትህም፣ ኑሮህም፣ መቀበሪያህም ኢትዮጵያ ውስጥ በመሆኑ! ለአንተ ከኢትዮጵያ ውጭ ሃገር ከኢትዮጵያዊንት ሌላ ማንነት ሊኖርህ አልወደድክምና ለጠላቶችህ የማትበገር መንፈስ፣ የማትታወክ ታጋሽ፣ ይልቁንም እንዲሁ በቀላሉ የማትቆጣና የማትነሳ ጀግና ባላንጣ ሆንክባቸው። ስለዚህም ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያዊንት ውጭ የሆነ ሃገርም ሆነ ማንነት በልክህ ያልተሰፋና የሚኮሰኩስህ ሆነውብህ ግፉን ሁሉ ታግሰህ እነሆ 25 የሰቆቃ አመታትን አሳለፍክ።

እኛ ግን እንዲህ እንመክራለን። የጎንደር፣ የጎጃም፣ የወሎ፣ የሸዋ ህዝብ ሆይ! አያቶችህ የኢትዮጵያዊነት ምንጭ፣ አባቶችህ የኢትዮጵያዊነት መሰረትና አፅኝ፣ አንተ ደግሞ የኢትዮጵያዊነት አንዱ ምሰሶና ጠባቂ ነህና በከንቱ አትታወክ! አማራነትም ወደ ኢትዮጵያዊነት ያሳደከውና ኢትዮጵያንም የከደንክበት የቀደመ ማንነትህ ነውና እንደ ባዕድ ነገር አትየው፣ ይልቁንስ እናቶችህ “ኩታ በየፈረጁ ይለበሳል” እንዲሉ ኢትዮጵያዊነትንም ሆነ አማራነትንም እንዴት ማስተናገድ እንዳለብህ እወቅበት።

ስለዚህ በህወሃትና በተላላኪዎች በየሄድክበት እንደ ጉድፍ የምትታፈሰውና እንደ ፋሲካ በግ የምትታረደው በ“አማራ” ስምህ በ“ኢትዮጵያዊ” ማንነትህ እንጂ በሌላ አይደለምና እነሆ “በቃ” ብለህ በአንድነት ዛሬ ቁም! አንተ ስትተባበርና በአንድነት ስትቆም ጠላቶችህ እንደሚርዱ ታውቃለህና እነሆ ለወልቃይት ጠገዴ ወገንህ ስትል ዛሬ በአንድነት ቁም! እንግሊዝ የሚርድለትን ቁጣህን፣ ጣሊያን የሚንበረከክለትን ሰይፍህን፣ ድርቡሽ የሚሸናለትን ክንድህን እነሆ ዛሬ አበርታ! የጉራፈርዳው፣ የበደኖው፣ የቤንቺው፣ ይጋምቤላው፣ የቤንሻጉሉ፣ ይበቃል በል! ዛሬም የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት “አማሮች” ድረስልን ይሉሃልና ድረስላቸው! በአማራነት መታረድ፣ በአማራነት መሰደድ፣ በአማራነት ….. ይበቃልና….!

ይድረስ ለጎንደር ህዝብ !

ባንዳውና ተላላኪው የተ.ሃ.ህ.ት ወራሪ ኃይል ከ 1972 ዓ.ም ጀምሮ ለም መሬቶችህን ለመንጠቅ ተከዜ ድንበርህን በማን አለብኝነትና በሃይል ተሻግሮ ከመጣ ወዲህ የወልቃይት የጠገዴና፣ የጠለምት ቤተሰቦችህ ላይ የፈፀመው እና እየፈፀመ የሚገኝውን የዘር የማጽዳትና በትግሪያዊነት የመተካት ወንጀል በተቻልህ ሁሉ ስትመክት ኖረሃልና ልትኮራ ይገባሃል።

እነሆ ዛሬም እብሪቱና ጥጋቡ ያልበረደለት ይህ ዘረኛና ተስፋፊ ቡድን “አማሮች” ነን ወደ ቀደመ የጎንደር/አማራ የአስተዳደር ክልል እንካለል ባሉና ኮሚቴ መርጠው፣ ፊርማ አሰባስበው፣ ህጋዊና ሰላማዊውን መንገድ ተከትለው ለታሪክና ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ ባቀረቡ ወገኖችህና ልጆችህ ላይ ለምን “ትግሬዎች” ነን አላላችሁም በሚል “እርምጃ እንወስዳለን” “ልክ እናስገባቸዋለን” የሚሉና የመሳሰሉ ዛቻዎችና ማስፈራሪያዎችን በግላጭ እየሰማን ነው።

ጀግንነት ማንነትህ ነውና ጨርቄን-ማቄን ሳትል በጀግንነትና በፅናት እራሱን በህወሃት ከተጫነበት “ትግሪያዊነት” ነፃ ለማውጣትና የአማራ ማንነቱን ለማስከበር ከሚታገለው የወልቃይት ጠገዴና፣ የጠለምት ወገኖችህ ጎን በመሰለፍ ከወራሪውና ከተስፋፊው የትግራይ ነፃ አውጭ ቡድን  መንግስታዊ ጥቃት ወገንህን፣ ሃገርህንና፣ ታሪክህን ትታደግ ዘንድ አደራችን ፅኑ ነው!

ይድረስ በዓለም ላይ ለምትገኙ የወልቃይት ጠገዴ  ተወላጆች !

ወራሪውና ተስፋፊው የትግራይ ነፃ አውጭ ቡድን ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ ሲፈፅምብን የነበረው የተቀነባበረና ኃይል የተሞላ የዘር ማጽዳት ወንጀል፣ በህዝባችን ላይ ያደረሰውን ሰቆቃና ግፍ የምንገልፅበት መንገድም ሆነ ቋንቋ እንደማናገኝለት እኛው የገፈቱ ቀማሾችና ሁሉን የሚያይ ሃያሉ እግዚአብሔር ብቻ ነው የምናውቀው።

ኢትዮጵያን በማፍረስ፣ ሃብቷን በመዝረፍና፣ ህዝቧን በማሳደድ የሰየጠነው ህወሃት፤ በዘር ፍጅትና፣ በወረራ የተለከፈው ተስፋፊው ህወሃት፣ ይልቁንም በንጹሃን ደምና በደካሞች እንባ መፍሰስ እድሜውን የሚያራዝመው ህወሃት፣ እነሆ ዛሬም የቀረውን ዘራችንን ፈጽሞ ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ፣ ክተት እያወጀና፣ መሪዎቹም በየመድረኩ  በግልፅ “የማያዳግም እርምጃ እንወስዳልን” “ልክ እናስገባቸዋልን” በማለት ሲዝቱብንና ሲማማሉብን የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ መላው ዓለም ይሰማቸዋል።

ይህ ሰሞኑን በህወሃት መሪዎች በኩል የሚታላለፈው ዛቻ ለእኛ በእጅጉ አሳስቦናል። የህወሃትን እብሪትና ጭካኔ ከእኛ ከግንባር ቀደም ገፈት ቀማሾች በላይ ማን ሊያውቀው ይችላል?

የሰሞኑ ህወሃታዊ ከበሮ ድለቃና ድንፋታ ሁለት አበይት መልዕክቶች ያዘለ ነው የሚል እምነት አድሮብናል።

1ኛ.  “የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ብሔር የማንነት ጥያቄ” በማንሳት “አማራ” መሆናቸውን በፊርማቸው ያረጋገጡትንና ኮሚቴ በመምረጥ ጥያቄያቸውን በህጋዊና በሰላማዊ መንገድ ባቀረቡ የወልቃይት ጠገዴ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ሲሆን። ይኸውም፦

  • ሰሞኑን እንደሚደረገው ሁሉ “የአማራ ብሔርተኝነት ማንነት” የመጠየቂያ ሰነድ ላይ “አማራ” ነን በማለት በፊርማቸው ያረጋገጡ ወገኖቻችን ላይ በተናጠል ወደ ፖሊስና የፍትህ ተቋማት በመጥራት በመንግስታዊ ዛቻና ማስፈራሪያ “ትግሬ” ነን በማለት እንዲፈርሙ ማስገደድ፤
  • በአቋማቸው የጸኑትን እንደተለመደው ሁሉ በማንኛውም መንግስታዊና ህዝባዊ ተቋማት አገልግሎት እንዳያገኙ በማድረግና በተለያዩ አሰልቺ ህወሃታዊ ዘዴዎች በማንገላታት “ትግሬ” ነን በማለት እንዲፈርሙ ማስቻል፤
  • “ድንበራችን ተከዜ ነው!” በማለት የተነሳውን ታሪካዊና ታላቅ ህዝባዊ ጥያቄ በመሸራረፍና “አንድ ጠገዴ” የሚለውን ጥያቄ ነጥሎ የመለሱ በማስመሰል ወልቃይትና ጠገዴን በመከፋፈል ማዳከም፤
  • በእነዚህና በሌሎች የማሰቃያና የማዋከቢያ ጫናዎች የማይንበረከኩትን ፅኑ ወገኖቻችን ደግሞ ከዚህ በፊት በሌሎች ክልሎች በሚኖሩ “የአማራ” ተወላጆች እንዳደረጉት ሁሉ ከሃገራችን/ከክልላችን ውጡ በማለት በካሚዮን እየጫኑ ከወልቃይት ጠገዴ ማባረር፣ ንብረታቸውን መውረስና ማውደም፣ ብሎም ቤቶቻቸውን ማቃጠል በቀጣይ የሚጠበቁ የህወሃት ፀረ-ህዝብ የሽብር መንገዶች ናቸው።

2ኛ. የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ብሔርተኝነት የማንነት ጥያቄን አንግበው የተነሱትን የኮሚቴ አባላት ኢላማ ያደረገ ሲሆን፣ ይኸውም፦

  • በተለያዩ መንገዶች በማስፈራራት፣ በመሬት፣ በገንዘብና፣ በተለያዩ ጥቅማጥቅሞች በመደለል፣ እራሳቸውን ህዝብ ከመረጠው ኮሚቴ አባልነት እንዲያገሉ ማባበል፤
  • በአቋማቸው ፀንተው እራሳቸውን ከኮሚቴ አባልነትና ከተነሱለት ጥያቄ የማያፈገፍጉትን በእስርና በድብደባ ሃሳባቸውን እንዲቀይሩ ማድረግ፤
  • በእስርና በድብደባ የማይንበረከኩትን የኮሚቴ አባላት በቤተሰብ ግፊትና የተለያዩ መንገዶችን በማመቻቸት ከሃገር እንዲሰደዱ ማስገደድ፤
  • በእነዚህና በመሳሰሉት የህወሃት የተለመዱ የመከፋፈያ ዘዴዎች የማይንበረከኩ የኮሚቴ አባላትን “እንገላችኋለን” በማለት ማስፈራራትና እንደቀደሙት ወንድሞቻችን እነዚህንም አፍኖ በመውሰድ አድራሻቸውን በማጥፋት ህዝባዊ ትግሉን ያለ መሪ በማስቀረት ለማኮላሸት የሚወሰድ ህወሃታዊ “እርምጃ” ሊኖር ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት አድሮብናል።

አበው “ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም” እንዲሉ፤ ይህ ዘራችንን ለማጥፋትና በትግሬያዊንት ለመተካት፣ ለም መሬታችንን ለመውረስና ሃገራችንን ለማፍረስ ቆርጦ የተነሳው የትግራይ ነፃ አውጭ ቡድን በሃይል የነጠቀን “የአማራ ማንነታችን ይጠበቅልን!” በማለት ለኢትዮጵያ ህዝብና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ህጋዊ ፊርማቸውን በማሰባሰብ በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ጥያቄ ያቀረቡ ቤተሰቦቻችን ላይ ያንዣበበውን ህወሃታዊ እልቂትና፣ መከራ ለመመከትና ለማኮላሸት ከምንግዜውም በላይ እንደ ቀደሙት አባቶቻችን በጋራና በአንድነት እንድንነሳ፣ ይልቁንም ከላይ ወገናዊ ጥሪ ላደረግንላችው ወገኖች ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ በማቅረብ ከህዝባችን ጎን እንዲሰልፉ በማስተባባርና በማቀናጀት ታሪካዊ ሃላፊነታችን እንድንወጣ ማሳሰብ እንሻለን!

ኢትዮጵያ ለዘላለም በክብር ትኑር!!

(ጎሹ ገብሩ፣ አባይ መንግስቱ፣ ገብሩ ማማይ፣ ቻላቸው አባይ፣ አበራ አታላይ፣ አብዩ በለው)

የካቲት 8, 2008 ዓ.ም

posted by daniel tesfaye

Advertisements

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: