FREEDOM 4 ALL ETHIOPIANS

FREEDOM,DEMOCRACY.JUSTICE.AND UNITY FOR ALL ETHIOPIANS …by DANIEL TESFAYE

‘አሸባሪ ብዕሮች’ ክንፉ አሰፋ

October 10, 2014 

ashebari-beroch-300x152ይህች አጭር ጽሁፍ የተወሰደችው በአውስትራሊያ ከምትታተም “አሻራ” ከተሰኘች መጽሄት ልዩ እትም ላይ ነው።

የፈረንሳዩ አንባገነን ገዥ የነበረው ናፖሊዮን ቦናፓርት በአንድ ወቅት ስለ ነጻ ፕሬስ ሲናገር “ከአንድ ሺህ ሻምላዎች ይልቅ አራት ጋዜጦች የበለጠ መፈራት አለባቸው።” ነበር ያለው።

አንባገነኖች ፕሬስን ይፈራሉ። ይጠላሉም። የህዝብ መሰረት የሌላቸው፤ በራሳቸው የማይተማመኑ ሁሉ ነጻ ሃሳብን ይጠላሉ። ነፍጥን ብቻ ተማምነው በሕዝብ ጫንቃ ላይ የሚቀመጡ፤ እንደምን ነጻ አመለካከትን ሊቀበሉ ይችላሉ? ፍጹም አንባገነናዊነት በሰፈነባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገሮች፤ ህግ አውጭው ህግ አስፈጻሚውን፣ ህግ አስፈጻሚው ደግሞ ህግ ተርጓሚውን እርስ-በርስ የሚቆጣጠሩበት እና የሚያስተከክሉበት አካሄድ የለም። ይህንን ቁጥጥር በጥቂቱም ቢሆን ተክቶ ይሰራ የነበረው ነጻው ፕሬስ ነው። ከዚህም አልፎ ሕዝቡ መብቱን እንዲያውቅና መብቱንም እንዲያስከብር ብዙ ሰርቷል-ፕሬሱ። ሙስናን አጋልጧል፣ እንደ እንባ ጠባቂም እየሆነ የህዝብን በደልም ይፋ አድርጓል። ይህን የተቀደሰ ተግባር ማከናወን እንደወንጀል፤ ጠንከር ሲል ደግሞ እንደ ሽብርተኝነት የሚቆጠርበት ሃገር ሆናለች የዛሬይቱ ኢትዮጵያ።

መብትን ማወቅ እና ማሳወቅ፤ ‘ህዝብ ለጦርነት እንዲነሳ ማድረግ፤ ወይንም በስራዓቱ ላይ ጥርጣሬ መፍጠር ነው’ ተብሎ ከተተረጎመ ደግሞ ጋዜጠኛን በአሸባሪነት መፈረጁ ብዙ ሊደንቀን አይገባም።
ኢትዮጵያ ላለፉት አስርት-አመታት ጋዜጠኞችን በማሰር ከአፍሪካ በቁጥር አንደኛ ደረጃ ላይ የነበረች ሃገር ናት። አሁን ይህንን ደረጃዋን ለቃለች። እድገትና ትራንስፎርሜሽኑን ተከትሎ ከመጡት ለውጦች አንደኛው መሆኑ ነው። ኢትዮጵያ የአንደኝነት ደረጃዋን ያጣችው ታዲያ ትራንስፎርሜሽኑ ይዞት በመጣው መሻሻል አይደለም። ነጻ ፕሬሱ ከሃገሪቱ እንዲጠፋ በተደረገ ሁለገብ ጦርነት እንጂ። አብዛኛው ጋዜጠኛ ተሰድዷል፣ ጥቂቶቹ ታስረዋል፣ አንዳንዶቹም አቅማቸው ተሟጦ አልቆ፤ ዝም ብለው እንዲቀመጡ ተደርገዋል። ለነጋሪ የተረፉትንም እስከዛሬዋ እለት ድረስ እያሳደዷቸው ይገኛሉ።

ከጅምሩ በፕሬሱ ላይ የተከፈተው የገዥው ፓርቲ ውግያ ቀላል አልነበረም። ፕሬሱ ግን እለት ተዕለት የሚያርፍበትን የአንባገነኖች ጡጫ ሁሉ ችሎ ብዙ ተጉዟል። እየተንገዳገደ፤ እየወደቀና እየተነሳ የህዝቡን የህሊና ንቃት እንዲሰፋ ከማድረጉም ባሻገር በኢትዮጵያ የማንበብ ባህል እንዲዳብር ነጻው ፕሬስ ተግቶ ሰርቷል። የህትመት ዋጋ እስከ 500% እንዲጨምር ቢደረግም ፕሬሱ አልቆመም ነበር። ጋዜጠኞች እንደጥጃ እየታሰሩ፣ እየተደበደቡ፣ እየተሰቃዩም ስራቸውን ላለማቋረጥ መትጋታቸውን አላቆሙም። በካድሬ ዳኞች ፍርደ-ገምድል ፍትህ ሲሰጣቸው፤ ያለ አግባብ በእስርና በገንዘብ ሲቀጡም ሰራቸውን አላቋረጡም…
የአሜሪካው ፍሪደም ሃውስ በተከታታይ ባወጣቸው ዘገባዎች ኢትዮጵያን ፕሬስ (Status: NOT FREE) “ነጻ ያልሆነች” ሃገር ሲል ፈርጇል። የፕሬስ አዋጁንም ፍጹም አፋኝ ሲል ይከሳል። የፈረንሳዩ ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ፣ የኒውዮርኩ ሲ.ፒ.ጄ. እና የብራስልሱ አይ.ኤፍ.ጄ. በሽብር ክስ የተያዙ የጋዜጠኖችን ሰነድ እያከታተሉ አሳፋሪነቱን ቢገልጹም አፍ እንጂ ጆሮ ከሌለው ስርዓት ያገኙት የስድብ ምላሽ ብቻ ነው። አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዋችም አፈናውን ይፋ ማድረጉን ተያይዘውታል። ከገዥው ፓርቲ የሚያገኙት ምላሽ “የኒዮ ሊበራል” አቀንቃኞች የሚል ስድብ እና ዛቻ ብቻ ነው።
ከምርጫ 97 ነኋላ ግን የህወሃት እድገት እና ትራንስፎርሜሽን፤ ጫን ያለ ነገር ይዞ ብቅ አለ።

ሽብርተኝነት!
ከዚህ በኋላ ጋዜጠኛ በህገ-መንግስት ሳይሆን፤ ህጉን በሚጻረረው አዋጅ መዳኘት እንዳለበት ተነገረ። ስርዓቱም በባሩድ ሳይሆን ይልቁንም በብእር ጫፍ እንደሚሸበር አረጋገጠ።
ይህ የሽብርተኝነት አዋጅ ቃል በቃል የተቀዳው ከአሜሪካ እና ከእንግሊዝ መንግስታት ሰነድ መሆኑን ሃይለማርያም ደሳለኝ ለቢቢሲ ሲናገሩ ተደምጠዋል። ድንቅ ነው። ሰውየው ግን ምን እየተናገሩ እንደሆን የሚያውቁት አይመስልም። በዚህች በሙት መንፈስ የምትመራ ሃገር ሌላም ብዙ እንግዳ ነገር እንሰማለን። የቡሽ አስተዳደር ከቶኒ ብሌየር ጋር አልቃይዳ የተባለውን አደገኛ ሽብርተኛ ለማጥፋት የነደፉት ይህ ሰነድ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኞችን ለማጥፋት እየተጠቀሙበት እንደሆነ ነው የሚነግሩን። የፈረንጆቹ ሽብርተኝነት (terrorism) ሲተረጎም፤ “በሃይማኖት ወይንም በርዕዮተአለም ጥላ ስር ተደራጅቶ አመጽን የማድረግ ተግባር” እንደሆነ ይነግረገናል።
በሽብርተኝነት ተወንጅለው በየእስር ቤቱ የተጣሉት የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች፤ የትኛውን ርዕዮተ-አለም ወይንም ሃይማኖት ተንተርሰው አመጽ እንደፈጠሩ፣ የትኛውን አውሮፕላን እንዳስጠለፉ፣ የትኛውን ህንጻ እንዳፈረሱ፣ የትኛውን ንጹህ ዜጋ እንደገደሉ አልተነገረንም።

እርግጥ ነው። የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች እየተቹ ይጽፋሉ። ትችቱ ታድያ ለውጡ ላይ አይደለም። የለውጡ አቅጣጫ ላይ እንጂ። አቅጣጫው ትክክለኛ መስመር መያዝ እና አለመያዙን መተቸት “ወንጀል ነው” ሲባል ለቀረው አለም አዲስ ነገር ሊሆን ይችላል። ከዚያ የባሰም አለ። ገዢውን ፓርቲ መተቸት እና ስለ ለውጥ አስፈላጊነት መጻፍ በሽብርተኛነት ያስከሰሰ ወንጀል ሆኖ ሰማን። አስቂኙ ነገር፤ አዋጁ ለኦሳማ ቢን ላደን ሽብር በምእራባውያን ሀገሮች የረቀቀ የጸረ-ሽብር ህግ መሆኑ ነው።

ጋዜጠኞች በሽብርተኝነት ሲፈረጁ ነው ነጻው ፕሬስ በኢትዮጵያ አፈር የለበሰው። ይህ የመጨረሻ ጥይታቸው መሆኑ ነው። አለማቀፍ የጋዜጠኞች ተሟጋች ተቋማት ሳይቀሩ ተስፋ የቆረጡ እስኪመስል ድረድ በዘንድሮ አመታዊ ዘገባቸው የኢትዮጵያን ጉዳይ ችላ ብለውታል። እነዚህ ተቋማት በየአመቱ ስለኢትዮጵያ ፕሬስ ሁኔታ የሚያወጧቸው ዘገባዎች የሚዘገንኑ ነበሩ። ወያኔን የማይማር፣ የደነዘዘ እና የማይለወጥ ስርዓት አድረገው ስላዩት ችላ ያሉት ይመስላል። ሃያ አመት የማይሰማ፣ ያሃ አመት የማይሻሻል፣ ሃያ አመት የማይማር ስርዓት… ውሃ ቢወቅጡት እንቦጭ ሆነባቸው።

በምርጫ 97 ሰሞን በርካታ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች ቃሊቲ ተወርውረው ነበር። በጉዳዩ ላይ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዲያሬክተር ከነበሩት ዶ/ር ማርቲን ሂል ጋር ስናወራ አንድ ጥያቄ አነሱልኝ።
“ለመሆኑ ሰርካለም ፋሲል ላይ ለምን እንዲህ ጨከኑባት? ” የሚል ነበር የማርቲን ጥያቄ። እኝህ ታላቅ ሰው ይህን ጥያቄ ለምን እንዳነሱልኝ አሁን ነው የተገለጠልኝ።
የሰርካለም ፋሲልን ጉዳይ ማንሳቱ የኢትዮጵያን ፕሬስ የሰቆቃ ጉዞ በከፊልም ቢሆን ይገልጸዋል።

ሰርካለምን ከባለቤትዋ እስክንድር ነጋ ጋር አፍነው ወደ ቃሊቲ ሲወስዷት ነብሰ-ጡር ነበረች። የመውለጃዋ ቀን ሲደርስም ከእስር አልለቀቅዋትም። በምጥ ስቃይ፣ ነብስ ውጭ፤ነብስ ግቢ ሁኔታ ውስጥ ሆና እንኳን አሳሪዎችዋ ርህራሄ አላሳዩዋትም ነበር። በመጨረሻ እዚያው ቃሊቲ እስር ቤጥ ናፍቆትን ተገላገለች። በዚያ የጭንቅ ወቅት የሚይዘውን እና የሚጨብጠውን ያጣ ስርዓት ምን እያደረገ እንደነበር እንኳን በውል አየውቀውም። “የመንግስት ጠላት” የሚል ታፔላ ተለጥፎለት የሚንቀሳቀስ ጋዜጠኛ፤ ሊወድቅ ከሚንገዳገድ ስርዓት ከዚህም በላይ ሊደረግበት እንደሚችል ለማስረዳት ሞከርኩ።

ነብሰ-ጡርዋ ሰርካለም የተከሰሰችው ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመናድ እና ለማፍረስ፣ ጥላቻን የምታስፋፋ፣ ጥርጣሬን የምትነዛ… ተብላ ነበር። በ “ምህረት” ከእስር እንደተፈታች ወደ ኬንያ ተሰደደች። በኋላም ሀገር ሰላም የሆነ ሲመስላት ከስደት ተመለሰች። ይህች ወጣት እትብትዋ ወደተቀበረባት ሃገርዋ ብትመለስም እንደዜጋ የመኖር ዋስትናዋ ግን በአንባገነኖች መዳፍ ስር ሆነ። በኑሮዋ እና በትዳርዋ ዙርያ ካለፈው የባሰ ችግር መጣባት። ባለቤትዋ እስክንድር ነጋ በሽብርተኝነት ተከሶ በፍርደ-ገምድል ዳኛ ለአመታት ተፈረደበት። ቤት ንብረታቸውም በግፍ ተቀማ። ከዚህ በኋላ በመኖር እና ባለመኖር የሚደረግ ምርጫ ውስጥ መግባት ግድ ሆነባት። እናም ባለቤትዋን ወህኒ ቤት ጥላ ዳግም ተሰደደች። እስዋም ሆነች በሰቆቃ የተወለደ ልጅዋ በመንገድ ከመወርወራቸው በፊት ያላቸው አማራጭ ይህ ብቻ ነበር። የሚወዷት ሃገራቸውን ጥለው ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ ስደተኛ ጋዜጠኞችን ተቀላቀሉ። እንደቀልድ የሚነገር ሌላም እውነታ አለ። ከ”ሽብርተኛ” ጋር በስልክም ሆነ በአካል ያወራ፣ አብሮ የታየ፣ አብሮ ሻይ የጠጣ፣ የተነካካ ሰው ሁሉ ሽብርተኛ እንደሆነ አዋጁ ይደነግጋል። ሰርካለም እና ናፍቆት በእስር ያለው እስክንድር ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ሽብርተኛ ተብለው ሊወነጀሉም ይችሉ ነበር።

በስልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ፍርሃት ውስጥ እንዳሉ ግልጽ ነው። በጋዜጠኛ የሚናድ ሀገ-መንግስት ይዘው ስንት አመት ሊዘልቁ እንደሚችሉ ባናውቅም፤ አሁንም ጋዜጠኞችን ሲያስሩ ይህንንኑ ዘፈን ይደጋግሙታል። 99.7 በመቶ በህዝብ የተመረጠ መንግስት መራጩን ሕዝብ ከቶውንም መፍራት አልነበረበትም። ነገሩ ስላቅ ነው። ይህ ቀልዳቸው ግን የህዝቡን ንቃተ-ህሊና ዝቅ አድርጎ ከመመልከት የሚመጣ ይሁን እንጂ ጉዳዪ ሌላ ነው። አንባገነኑ ናፖሊዮን ቦናፓርት ብሎታል። ከሺ ሳንጃ አንድ ጋዜጠኛ ያስፈራል። የጭቆና እና የአፈና ስርዓት ገንብቶ ለረጅም አመት የቆየ አንባገነን በታሪክ አልታየም።
የፈቀደውን መምረጥ የሚችልን ህዝብ አዲስ ዘመንን ብቻ እንዲያነብ መምከራቸው ብቻ አይደለም በሕዝብ ላይ ያላቸው ንቀት፤ የፍትህ ስርዓቱን ለበቀል የሚዘረጋ እጃቸው አድርገው ነጻውን ፕሬስ ለማጥፋት ሲጠቀሙበትም እጅግ ያንገበግባል። የህግ የበላይነትን እንዲህ እያደረጉ ናዱት።

ኢሕአዴግ የፕሬስ ነጻነትን ለህዝቡ እንዳጎናጸፈ ይመጻደቃል። ይህ ስህተት ነው። መናገር፣ ሃሳብን በነጻነት መግለጽ፣ መጻፍ፣ … ወዘተ መብት የሰው ልጅ የተፈጥሮ ጸጋ እንጂ አንድ ስርዓት የሚያጎናጽፈን ጉዳይ አይደለም። በሌላ በኩል ደግሞ ይሀው ስርዓት እነዚሁኑ መብቶች እየጨፈለቀ እነሆ ሃያ ሶስት አመታትን ዘልቋል።
ነጻ ፕሬሱን ለምእራባውያን የዲሞክራሲ ማሳያ አድርጎ እንደተጠቀመበት እርግጥ ነው። የአለም ባንክ እና ለጋሽ ሃገሮች በኢትዮጵያ የሳንሱር አዋጅ እንደጠፋ ነው የሚነገራቸው። የእርዳታና ብድር እጃቸውን የሚዘረጉልንም ከቀድሞው የተሻለ የመጻፍና የመናገር ነጻነት አለ ብለው ስለሚያምኑ ይመስላል። ግና ይህ የሳንሱር አዋጅ በአእምሮ ሳንሱር መተካቱን የምናውቀው እኛ ብቻ ነን። ሳንሱር ቢኖር ይህ ሁሉ ጋዜጠኛ ባልታሰረ፣ ባልተንከራተተ እና ባልተሰደደ ነበር።

ምርጫ መጣ! ጋዜጠኛ ይውጣ! እንዲሉ… በቅርቡ በስድስት ነጻ ፕሬስ ህትመቶች ላይ ከተመሰረተው ክስ ጋር በተያያዘ አስራ ሁለት ጋዜጠኞች ለስደት መብቃታቸው ተዘግቧል። በጭላንጭል የነጻነት ድባብ ይንቀሳቀሱ የነበሩት፤ አዲስ ጉዳይ፣ ሎሚ፣ ጃኖ፣ አፍሮ ታይምስ እና እንቁ ጋዜጦች እንዲቋረጡ ተደርጓል። ጋዜጠኞቹም በአሸባሪነት ሽፋን ተከስሰው እስከ አስራ ስድስት አመት የሚደርስ ጽኑ እስራት ተበይኖባቸው የነእስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ እና ርእዮት አለሙ እጣ ይደርሳቸዋል። እነዚህ ጋዜጠኞች የነበራቸው አማራጭ የሽብር አዋጁ ሰለባ መሆን አልያም አገር ለቀው መሰደድ ነው። ተሰደዱ። የስደተኛ ጋዜጠኛውን ቁጥር ወደ 210 አሳደጉት።
ውንጀላው ግን በተያዘለት መርሃ-ግብር ቀጥሏል። ሰሞኑን “ያልተገሩ ብዕሮች” በሚል ርእስ በኢቲቪ የቀረበውን “ዘጋቢ ፊልም” ያስተውሏል? በአንድ በኩል የጋዜጠኖቹ ጉዳይ በህግ የተያዘ እንደሆነ ይነግሩናል። በሌላ በኩል ደግሞ “ልማታዊ” ተዋንያን እና የስርዓቱ አጎብዳጆችን በመገናኛ ብዙሃን አቅርበው ፍርድ እንዲሰጡ ያደርጓቸዋል። በእርግጥ በመገናኛ ብዙሃን እየቀረቡ አንድ ተጠርጣሪን በወንጀለኝነት መፈረጅ አዲስ ነገር አይደለም። የፍትህ አካሉ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ተጠርጣሪው በኢቲቪ የፖለቲካ ፍርድ ይበየንበታል። ከዚያም እንደ “ዳኛ” ልዑል አይነት የሲቪል ሰርቪስ ምርቶች ውሳኔውን ያጸኑታል።

በዚያ የኢቲቪ ቅንብር ሃይሌ ገብረስላሴም ተዋንያን ነበር። የሚናገረውም የትዬለሌ። “ትልቁ የጦር መሳርያቸው ፕሬስ ነው።… ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ይባላል… ” ይለናል ሃይሌ ገብረስላሴ። “ዘጋቢ” ፊልሙም የእነ እስክንድር ነጋን ፎቶ፣ የእነ ተመስገን ጽሁፎች ያሳየናል። የዚህ ድራማ ሌሎቹ ተዋንያን ከሙያው ጋር የተያያዝን ነን የሚሉ አድርባዮች ናቸው። ሃይሌ ግን ምን ቤት እንደሆነ ግልጽ አይደለም። በየትኛውስ እውቀቱ ነው ፍርድ ሊሰጥ የደፈረው? “አንድ ጋዜጣ የውሃ አምራች ድርጅትን እንዲዘጋ አድርጓል።” ሲል ሃይሌ በዚያ “ዘጋቢ ፊልም” ይወነጅላል። አንድ ጋዜጠኛ እውነትን ጽፎ የንግድ ድርጅትን ወይንም የመንግስት ተቋምን ማፍረስ ወይንም በተቋማቱ ላይ ጥርጣሬ መፍጠር ከቻለ እንዲያውም ጀግና ነው የሚባለው። ጋዜጠናው የሚጽፈው ውሸት ከሆነ ደግሞ ፍርዱን ለህዝቡ ለምን አይተውለትም?
አብራሃ ደስታ ሌላው በአሸባሪነት ሽፋን የተከሰሰ ጋዜጠኛ ነው። አብርሃ አሸባሪ መሆኑ የተረጋገጠው ፍርድ ቤት ሲገባ እና ሲወጣ ነው። ሲገባ በጭብጨባ ሲወጣ በጭብጨባ ተሸኝቷል። ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ኣብርሃ ጀግና! የነፃነት ታጋይ! እንወዳሃለን፤እናከብርሃለን ሲለው እነ ሃይሌ ገ/ስላሴ የት ነበሩ?

ያልተገራ አንደበታቸውን በመገናኛ ብዙሃን ሲከፍቱ የነበሩት እነዚህ ተዋንያን የሚነግሩን እጅግ አሳፋሪ ነገር ነው። አጠቃላይ ይዘቱ በመንግስት ላይ ምንም አይነት ትችት መቅረብ የለበትም የሚል እንድምታ አለው። የህወሃትን አንባገነናዊነት መተቸት፣ የስርዓቱ ፖሊሲዎች መንካትና በባለስልጣናቱ ላይ ጥርጣሪ እንዲኖር ማድረግ… ስርዓቱን ያፈርሰዋል ነው እያሉን ያለው። ህግ አውጭው ከህግ አስፈጻሚውን፣ ህግ አስፈጻሚው ደግሞ ህግ ተርጓሚውን እርስ-በርስ የሚቆጣጠሩበት እና የሚያስተከክሉበት አካሄድ በሌለበት ሃገር ነጻው ፕሬስ ከዚህ ውጭ ምን ይስራ ነው የሚሉት? ፕሮፓጋንዳ?

ለፕሮፓጋንዳውማ በርካታ አማራጮሽ አሉ። አዲስ ዘመን ጋዜጣም አለልን። ለ90 ሚሊዮን ህዝብ የቀረው ጋዜጣ። አዲስ ዘመን በቁጥር ስንት ሺ እንደሚታተም ባናናውቅም በኪሎ እየተሸጠ የሸቀጥ እቃ መጠቅለያ ሆነ እንጂ። ‘የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተመረቁ፣ ሃይለማርያም ደሳለኝ ወደ ሱዳን ሄዱ፣ ሃይለማርያም ደሳለኝ ከሱዳን ተመለሱ። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ 11 እጅ እንደሚያድግ ሃይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ።’ …. የሚሉ ዘገባዎችን እየያዘ ከሸቀጥ እቃ መጠቅለያነት ውጭ ለሚመጻደቁለት እድገት ምንም እንዳልፈየደ እንኳ አያውቁትም።

የመገናኛ ብዙሃን አፈናው በነጻ ፕሬሱ ላይ ብቻ አልተገደበም። በኢትዮጵያ የመረጃ መረቦችም ታፍነዋል። ከሰብ ሰሃራ አፍሪካ በኢንተርኔት ይዞታ እና አገልግሎት የመጨረሻዋ ሃገር ናት። ኢንተርኔቱን የሚቆጣጠረው መንግስታዊው ቴሌኮም ስርዓቱን የሚተቹ ድረ-ገጾችን በቻይና ቴክኖሎጂ እንዲዘጉ አድርጓል። የዜጎችን ስልክ በህገወጥ ማንገድ መጥለፍ የተለመደ ተግባር ነው። እንዲሁም ስካይፕ እና ቫይበር ያሉ የቮይስ ኦቨር ስልኮች ደግሞ ፊን ፊሸር በተባለ የኮምፒዩተር ቫይረስ አማካኝነት ይጠለፋሉ። እንዲህ እያሉ በዜጎች የግል ህይወት ሳይቀር እየገቡ ቴሌን ሙሉ በሙሉ የስለላ ተቋም እንዳደረጉት የአሜሪካው ሂዩማን ራይትስ ዋች ይፋ አድርጓል።
ኢትዮጵያን ወደ ጨለማ ዘመን እየወሰዳት ያለው ይህ የህወሃት ስርዓት የኢንተርኔት ተጠቃሚው እንዲያሽቆለቁል እየጣረ እንደሆነ ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት። በተለይ የፌስቡክ አብዮትን ለመግታት ስለሚሻ የኢንተርኔት አገልግሎትን ማዳከሙ ላይ ጥብቅ አቋም ይዟል። መንግስት አልባዋ ሶማልያ እንኳን፣ ስድስት የቴሌፎንና ስልክ አቅራቢ ኩባንያዎች አሏት። በዚህ ቀላል ቴክኖሎጂ እንኳን ከሶማልያ በታች ሆኖ ስለ እድገት መመጻደቃቸው ሊያፍሩበት ይገባል።

እጅግ የሚያሳዝነው ይህ ስርዓት ለፈጸመው ለዚህ ሁሉ በደል ለሽልማት መብቃቱ ነው። ልማታዊው አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ በአርቲስቶች ስም ለሟቹ ጠቅላይ ሚ/ር የወርቅ ብዕር ነበር ያበረከተላቸው። ብዕር ትልቅ ትርጉም አለው። ብእር የሚሸለም ሰው ለፕሬስ ክብር ያለው፤ ፕሬስን የሚያከብር ሰው ነው። ሰራዊት የወርቅ ብዕር እንዲሸልም አርቲስቶች አልወከሉትም ነበር። ይህንን ሲያደርግ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች እስር ቤት ውስጥ ይንገላቱ ነበር። ሰራዊት ይህንን ሲያደርግ የአለም አቀፍ ህብረተሰብ ጠ/ሚኒስትሩን የፕሬስ አፈና በእጅጉ ያወግዝ ነበር። እንደ ሰራዊት ያሉ ሃላፊነት የጎደላቸው ሰዎች ብዙ አይደሉም። ለህሊናቸው ሳይሆን ለሆዳቸው ሲሉ እንዲህ አይነት ስራ እየሰሩ በሰው በቁስል ላይ እንጨት ይሰድዳሉ። ታዲያ እንደነዚህ አይነቶቹ አድርባዮችም ለፕሬሱ መጥፋት ሚናቸው ቀላል አይደለም። የማያልፍ የለም። ሁሉም ያልፋል። መንግስትም እንደ አንሶላ ተጠቅልሎ ይሄዳል። ይህ ቀን አልፎም ለትዝብት ያበቃናል።

ማን ነበር “ፕሬስ የሌለው መንግስት ከሚኖረን መንግስት የሌለው ፕሬስ ቢኖረን እንመርጣለን።” ያለው? እርግጥ ነው። ያለ ፕሬስ የሚኖር ህዝብ በጨለማ ነው የሚጓዘው። ያለ ነጻ አስተሳሰብ እና ያለ ነጻ ፕሬስ፣ እድገት ይመጣል ማለት አይታሰብም። እንዲያው የህዝብን ንቃተ-ህሊና ዝቅ አድርጎ መመልከት ይሆናል እንጂ።

posted by Daniel tesfaye

Advertisements

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: