FREEDOM 4 ALL ETHIOPIANS

FREEDOM,DEMOCRACY.JUSTICE.AND UNITY FOR ALL ETHIOPIANS …by DANIEL TESFAYE

የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው እስከዛሬ የት ነበር? (ድምፃችን ይሰማ )

35151fd67b1e0d781375561649
August 29, 2013
መንግስት በካድሬዎቹ የማስገደድ ዘመቻ እየፈጸመለት ያለው የፊታችን እሁድ የተጠራው ሰልፍ በሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የተጠራ መሆኑ መገለጹ ይታወሳል፡፡ ተቋሙ የሰልፉ አላማ አክራሪነትን ለማውገዝ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ካሁን ቀደም ሲፈጠሩ በነበሩ አገራዊ ችግሮች ላይ መፍትሄ ፍለጋ ሲንቀሳቀስ እምብዛም የማይታይ ተቋም ዛሬ በድንገት የመንግስት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ቅጥያ በሆነ ድርጊት ውስጥ ዘው ብሎ መግባቱ ግን ብዙ ጥያቄዎችን እያስነሳበት ይገኛል፡፡ ከጥያቁዎቹ ጥቂቶቹን ከታች እንያቸው…Ethiopian Musilms

ከሁለት አመታት ወዲህ የመንግስት ባለስልጣናት በግልጽ በሙስሊሙ ሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ ሲገቡ ታይተው ነበር፡፡ ዶክተር ሽፈራውን የመሳሰሉ ባለስልጣናት በእስልምና ቀኖናዎችና አስተምህሮቶች ጣልቃ ገብተው ፈትዋ ሲሰጡና በመጅሊሱ ጀርባ ተሸፍነው የግዳጅ ስልጠናዎችን ሲያዘጋጁ ነበር፡፡ የመስጂድ ኢማሞች ‹‹ስልጠና ካልገባችሁ ትባረራላችሁ›› እየተባሉ ሲገደዱ፣ ‹‹ስልጠና ሳትጨርሱ ከካምፕ አትወጡም›› እየተባሉ ለህክምና እንኳን በፖሊስ ታጅበው ሲላኩና ጁምአ መስጂድ ሄደው መስገድ ሲከለከሉ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው የአባቶችን ክብር መደፈር አላወገዘም፡፡ ‹‹ይሄ ነገር ተገቢ አይደለም›› ሲል አልገሰጸም፡፡ የሱ ትልቁ ስራ ይሄ አልነበረምን? ታዲያ ዛሬ ከየት መጥቶ ነው አክራሪነት አስግቶኛል ብሎ ከመንግስት ጎን የተሰለፈው?

ህዝበ ሙስሊሙ ላይ የሚደረጉ የመብት ጥሰቶች ከቀን ወደቀን እየገዘፉና እየተበራከቱ ሲመጡ ቆይተዋል፡፡ የህዝበ ሙስሊሙ አንድነት ጠንክሮ በሚታይባቸው ከጁምአ ሰላት በኋላ በሚደረጉት ተቃውሞዎች ማብቂያ በተደጋጋሚ ወጣቶች በደህንነትና ካድሬዎች ጥቆማ ታፍሰዋል፡፡ ያለምንም ማስረጃ በየጣቢያዎቹ ተንገላተዋል፡፡ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ከ250 ቀናት በላይ የታሰሩ እስረኞች ነበሩ፡፡ በጣቢያዎች ውስጥ ደግሞ ቀለባቸው ድብደባ፣ ማንጓጠጥና ሃይማኖታቸውን ማናናቅ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሙስሊም ላይ በየጁምአው ህገወጥ የሆነ የጅምላ እስር ሲፈጸም የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው እኔ ጥላ የሆንኳቸው አማኞች ተበደሉ ብሎ አንድም መግለጫ አውጥቶ፣ ባለድርሻ አካላትንም ገስጾ አያውቅም ታዲያ ዛሬ ምን ታየኝ ብሎ አደባባይ መውጣትን ናፈቀ?

መሪዎቻችን ህዝበ ሙስሊሙን ሰብስበው መያዝ የቻሉና ለእንቅስቃሴያችን ሰላማዊነትም ሊተካ የማይችል ሚና የተጫወቱ ድንቅ ለአገር አሳቢ ዜጎች ነበሩ፡፡ ህዝቡ ቁጣውንና ስሜቱን ዋጥ አድርጎ አገርን ከሚጎዳ አካሄድ እንዲቆጠብና ተቃውሞውን በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲገልጽ በማድረግ ለኢትዮጵያችን ትልቅ ውለታ ፈጽመዋል፡፡ እኒህን የመሳሰሉ ተምሳሌታዊ ዜጎች ያለአንዳች ጥፋት በጅምላ ሲታሰረሩና ማእከላዊ ሲቆለፍባቸው፣ እንዲሁም ያልሰሩትን ‹‹ሰርተናል›› ብለው እንዲያምኑ ለማድረግ አሰቃቂ የሆነ ቶርቸር ሲፈጸምባቸው አንዳችም ተቃውሞ ያላሰማው የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዛሬ ከየት መጥቶ ይሆን ለፖለቲካ ትርፍ የተጠራ የግዳጅ ሰልፍ አቀናባሪ ሀኖ የሚገኘው?

ከቀን ወደቀን እየጋለ የሚመጣውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማስቆም በሚል መንግስት በተለያዩ ወቅቶች የሃይል እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ በአሳሳ 4 ሙስሊሞች እንደቀልድ ተገድለው ሌሎች በርካቶችም ቆስለዋል፡፡ መንግስት ግን ‹‹የገደልኩት አሸባሪዎችን ነው›› የሚል መግለጫ ለመስጠት አፍታም አልፈጀበትም፡፡ ደሙ የፈሰሰ ህዝብ ላይ እንዲህ ስነልቦና የሚያደማ ውንጀላ ሲፈጸም የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው አንድ እንኳ ትንፋሽ አልተነፈሰም፡፡ ‹‹ዜጎች ለምን ይሞታሉ?›› አላለም፡፡ መንግስት በደቡብ ወሎ ላይ በወሰደው ተከታታይ ዘመቻ ሌሎች በርካቶችን ሲገድልና ሲያቆስል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች አገር ጥለው ሲሰደዱ እና የሃይማኖት አባቶች ሲንገላቱ ‹‹ይሄ ነገር ገደብ ይበጅለት›› ሲል ያልመከረ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምን ሰራሁ ሊል ይችላል? ሐረር ላይ በጁምአ ተቃውሞ መሐል ፖሊሶች የጥይት እሩምታ አዝንበው አንድ ህጻንና አዋቂ ሲገድሉ፣ ሺዎችን ሲደበድቡ ጉባኤው የት ነበር? አወሊያ መስጂድ በአድማ መበተኛ ጭስ ሲታፈን፣ ምግብ የሚያበስሉ እናቶች ተደብድበው በጭነት መኪና ሲጫኑ፣ ሴት እህቶቻችን በሌሊት በድልድይ ላይ ሲገፈተሩ በሃይማኖት አባቶች የተሞላው ጉባኤ ከቶ የት ነበር?

የተራድኦ ድርጅቶች እንደኢትዮጵያችን ባሉ አዳጊ አገራት የድሀውን ኑሮ ለመደጎም አስፈላጊ ተቋማት ናቸው፡፡ ለህብረተሰቡ የሚሰጡት ዘርፈ ብዙ አገልግሎትም መተኪያ የማይገኝለት ነው፡፡ በመንግስት ህገ ወጥ ዘመቻ የህዝበ ሙስሊሙ ተቋማት በገፍ ሲዘጉና ሲታገዱ፣ ለአመታት የተለፋባቸው ድርጅቶች መና እንዲቀሩ ሲደረግ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው አንዳችም ያለው ነገር የለም፡፡ ባገር ወግና ስርአት አጥፊን ወቅሶ አላሸማገለም፡፡ ድምጹ ባስፈለገን ሰአት ያጣነው ይኸው ተቋም ግን ዛሬ በፖለቲከኞች የተጠራ ሰልፍ አዘጋጅ ሆኖ እያየነው ነው? የታለ ታዲያ ታማኝነቱ? የታለ ለመርህ ተገዢነቱ?

መንግስት ህዝበ ሙስሊሙ ላይ የተቀናጀ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ከጀመረ ቆይቷል፡፡ በተደጋጋሚ በሚዲያዎች ህዝበ ሙስሊሙን ጥላሸት በመቀባት፣ ለአገር ስጋት አድርጎ ማሳየትና ከሌላው ወገን ጋር ለማቃቃር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ህዝብን ከህዝብ ለማጫረስ አደገኛ መርዝ ተረጭቷል፡፡ ይህ ሁሉ አደጋ ሲያንዣብብ ግን ኢትዮጵያዊው ህዝብ ለዘመናት በኖረበት የመቻቻል ባህሉ የጥላቻ ወጀቡን ተቋቁሞ አለፈው እንጂ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው ግን አንዳችም ያለው ነገር አልነበረም፡፡ ‹‹ተዉ ይሄ አካሄድ በታሪክ ያስወቅሳል መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ሊገባ አይገባም›› የሚል ግሳፄ የማይሰጥ ተቋም ታዲያ ምነው ዛሬ ለአደባባዩ ከፊት መሰለፍ መረጠ?

አዎን! በእርግጥም ህዝብ ሲሰደብ፣ ሲታሰር፣ ሲገረፍ፣ ሲደበደብ፣ ሲገደልና ሲሰደድ አንዳችም መናገርና መገሰጽ ያልቻለ የሃይማኖት አባቶች የጋራ ተቋም የቆመለት አላማ በአደባባይ ሲጣስ መደበቅን መርጡ ከቆመለት አላማ ውጭ ከበዳዮች ጋር ሲሰለፍ ማየት የሚያሳዝን እውነታ ነው! ከተቋሙ ጀርባ ያለውን ረጅም እጅ እንድንማትርም ያለጥርጥር ያደርጋል! አንድ ነገር ግን እንበል በዚሁ ጉባኤ ስም የተጠራው ሰልፍ ግዚያዊ ሽፋኑ አክራሪነትን መቃወም ነው ተብሏል፡፡ የህዝበ ሙስሊሙ የመብት ጥያቄ የትኛውንም ሁኔታዎች በጭፍን መከተልን እና በጭፍን ማግለልን እንደስልት ተከትሎ አያውቅም፡፡ የእሁዱን ሰልፍም እንደከዚህ ቀደሙ በጥልቀት ይፈትሸዋል በአላህ እገዛም ለጉዟችን መልካምን ይወስናል፡፡

አላሁ አክበር!

source,,,,http://ecadforum.com/Amharic/archives/9591/

posted by Daniel tesfaye

Advertisements

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: